Gumii Paarlaamaa Oromoo (GPO)

Oromo Parliamentarians Council (OPC)

 

Baga Nagaan Dhuftan!Welcome to Oromo parliamentarians council!

 

 

 

 

 

 

 

 

 

              New Page 2 home                         

"በኦህዴድ ቁርጠኝነት ማነስ ምክንያት የኦሮሞ ህዝብ ህልውና ለከፍተኛ አደጋ የሚጋለጥበት ጊዜ ላይ ደርሷል።"


የኦሮሞ ህዝብ ለረጅም ዘመናት በገዛ አገሩ ላይ የባርነትን ቀንበር ተሸክሞ ኖሯል። በሚሊየን የሚቆጠር የኦሮሞ አርሶ አደር ከመሬቱ ተፈናቅሎ ድንጋይ ለመፍለጥና የሰው ፊት ለማየት ተገዷል። ሀብት ጥሪቱን ተዘርፎ በድህነት ሲማቅቅ ዘመናት አስቆጥሯል። ኦሮሞ በመሆኑ ብቻ ያለምንም ጥፋት በሸፍጥ ሲወነጀል፤ ሲገደልና ሲታሰር ትውልድ በትውልድ ተተክቷል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ልጆች በወያኔ ደህንነት ነጭ ለባሾች ታፍነው የዉሃ ሽታ ሆነዋል። በጨቋኞች ፈርጀ ብዙ ሴራዎች በሚከፈትበት ወራራ ምክንያት ያባት ያያቶቹ እትብት ከተቀበረበት ቀዬው ተፈናቅሎና አውላላ ሜዳ ላይ ተበትኖ በረሃብና በእርዛት አለንጋ እየተገረፈ የሰቀቀን ህይወት ለመግፋት ተገዷል። እልፍ አዕላፎች በኦሮሞነታቸው ብቻ በሸፍጥ ተወንጅለው ሲታደኑ፣ በገዛ አገራቸው ላይ ምድር ጠቧቸው፣ ስደት ምርጫ የሌለው መፍትሔ ሲሆንባቸው ተሰደው፣ በሰው አገር ባይተዋር ሆነው መከራዎችን ለማስተናገድ ተገደዋል። ብዙ ሺዎች ወድ ህይወታቸውን ለዓሳ ነባሪ ገብረዋል።
-
"ሰላም ወዳዱ የኦሮሞ ህዝብ ለረጅም ዘመናት በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ ያለምንም ጥፋት በገዛ ቀዬው መወረር መገደሉ እንዲቆምለት ሲጠይቅ ቆይቷል። መንግስት ግን ለኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ተገቢውን መልስ ባለመስጠቱ ትዕግስቱ ያለቀበት ህዝባችንም መብቱን ለማስከበር ክንዱን አፈርጥሞ ለትግል ታጥቆ መነሳት አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ተረዳ። በተለየ መልኩ ደግሞ ከአምባገኑ የወያኔ የጭቆና ቀንበር መላቀቅ የሚቻለው በትግልና በትግል ብቻ መሆኑን በጥልቀት የተረዳው የቁቤ ትውልድ ባለፉት አራት ዓመታት ራሱ ከፊት ተሰልፎና ሰፊውን የኦሮሞ ህዝብ ከኋላው አስከትሎ ባቀጣጠለው የነጻነት ትግል፤ ወደር የሌለው የህይወትና የደም መስዋዕትነትን ቢከፍልበትም፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የወያኔ አገዛዝን እጅ ለመጠምዘዝ ችሏል። ውድቀቱ አይቀሬ መሆኑን የተረዳው የወያኔ አምባገነን ቡድንም በተዘዋዋሪ መንገድ ህልውናውን ለማስቀጠል የሚያስችለውን ሌላ አምባገነን ለመተካት መላ ዘየደ። እናም ወያኔ ሳይወድ በግዱ፤ ኦህዴድን ፈርቶ ሳይሆን በኦሮሞ ህዝብ ፈርጣማ ክንድ ተገዶ የአገሪቷን የፖለቲካ ሥልጣን የበላይነት ልጓም የወያኔ ውልድ ለነበረው ኦህዴድ አስጨበጠ።
-
"እናም የኦሮሞ ህዝብ የወያኔዎችን የጭቆና መረብ በጣጥሶና ገፍቶ ገደል አፋፍ ባደረሰበት ወቅት እነ አቶ ለማና እነ ዶ/ር አብይ የኦሮሞ ህዝብ እራሱን ብቻ ሳይሆን ኦህዴድንም ጭምር ነጻ እንደሚያወጣ ስለተረዱ፤ አሰላለፋቸውን በማስተካከል የህዝብን ትግል ነጥቀው ማስተጋባት ጀመሩ። በመቀጠልም «ጌታችን የኦሮሞ ህዝብ ነው፤ ህዝባችን ጊዜ ይስጠን» በማለት ህዝባችንን ተማጸኑት። የትግሉ ዋና ዓላማ ነጻነት እንጂ የፖለቲካ ድርጅትን ማማረጥ እንዳልሆነ አጥብቆ የሚያምነው፤ ይቅር ባዩና የዋሁ ህዝባችንም፤ ለሀያ ሰባት አመታት የወያኔ ቀኝ እጅ ሆኖ ሲገድለው፤ ሲያስገድለው፤ ሲዘርፈው፤ ሲያስዘርፈውና ሲያደማው ለቆየውና አዝማሚያውን አይቶ አሰላለፉን ላስተካከለው ኦህዴድ ያለማንገራገር የተጠየቀውን ጊዜ ሰጠው። የኦህዴድ አውራዎችም ይህን ወርቃማ እድል በመጠቀም ያገሪቷን የፖለቲካ ስልጣን ጨበጡ። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ የኦሮሞ ህዝብ እየተገደለና እየተፈናቀለ፤ ለኦህዴድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ህይወቱንም ጭምር እየሰጠው እስከ ዛሬ ቆይቷል።
-
"የቁቤ ትውልድ ሆይ! ሰፊው የኦሮሞ ቄሮና የኦሮሞ ህዝብ ሆይ! “የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም” እንደሚባለው ሁሉ እነሆ ዛሬም ኦህዴድ ያገሪቷን የፖለቲካ ሥልጣን በጨበጠበት ጊዜም ህዝባችን በገዛ ቀዬው መወረር መገደሉ አልቀረለትም። ብዙ ታግሰናል። ብዙ ብዙ ጠብቀናል። ቀን በቀን የወገኖቻችንን ውድ ህይወት እያጣን እስከ ዛሬ ለኦህዴድ ጊዜ ሰጥተናል። በኦሮሚያና ሱማሌ አዋሳኝ ወረዳዎች በየቀኑ የወያኔ ቅጥረኞች አረር ህዝባችን ላይ መዝነቡን ቀጥሎበታል። እንደ ፋሲካ በግ በሰቅጣጭና ዘግናኝ ሁኔታ በካራ መታረዳችን ቀጥሎበታል። በየቀኑ እያለቀስን ሬሳ መቅበር መደበኛ ክስተት ሆኗል። የኦሮሞ እናቶች ለቅሶ ቀን በቀን ማስተጋባቱን አላቋረጠም። ፋታ የሌለው የህዝባችን ጩሀትም ሰሚ ጆሮ አጥቷል። 
-
“ጌታችን ህዝባችን ነው» ያሉት እነ አቶ ለማና ዶ/ር አብይም በ”ጥልቅ ተሀድሶ” ስትራቴጂያቸው ባለፉት አራት ዓመታት በቀበሌ፣ በወረዳና በዞን ደረጃ በቄሮዎች ትግል የፈራረሰ ኮረጆ ገልባጭ መዋቅራቸውን መልሰው ለማደራጀት ከመራወጥ ባሻገር ወያኔ ያነጣጠረባቸውን አደጋ እንኳን ለማየት አልቻሉም፡፡ ለህዝባችን ጩሀትም የዝሆን ጆሮ ይስጠን ብለዋል። በቄሮ የትግል ሰደድ ምድር ሲጠባቸው ምለው ተገዝተው ለህዝባችን የገቡትን ቃል በልተዋል። ኦህዴድ በሰጠነው ጊዜ ተጠቅሞ ቆራጥ አቋም ይዞ ከህዝባችን ትግል መቀላቀል ባለመቻሉ እራሱም ህልውናውን ለወያኔ ሴራ አጋልጧል፡፡ 
-
"ባሁኑ ጊዜ የተጋረጠብን አስከፊ አደጋ ደግሞ ጎጠኛው የወያኔ ቡድን የኦህዴድንም ሆነ የኦሮሞ ህዝብን ህልውና ለማጨለም ታጥቆ መነሳቱ ነው፡፡ ኦህዴድ የኦሮሞ ህዝብ የሰጠውን ጊዜ በአግባቡ ሊጠቀምበት አልቻለም፡፡ ማስመሰል እንጂ በሙሉ ልብ የኦሮሞ ህዝብን ትግል አልተቀበለም፡፡ ህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን ወረራና ግድያ ሊያስቆም አልቻለም፡፡ ይህ የኦህዴድ ቁርጥ አቋም መውሰድ አለመቻል ለወያኔ ማገገም ዕድል ስለሰጠው እነሆ አሁን ኦህዴድ በራሱ ላይ አደጋ እንዲጋብዝ አድርጎታል፡፡ እኛ ጊዜ ስንሰጠው ባላዋቂነት ለወያኔ የማገገሚያ ጊዜ በመስጠት በራሱና በህዝባችን ላይ አደጋ እንዲጋረጥ ለማድረግ በቅቷል፡፡ ኦህዴድ ህዝባችን የሰጠውን እድል ተጠቅሞ በሙሉ ልቡ ከኦሮሞ ህዝብ ትግል ጉን ቆሞ ቢሆን ኖሮ በቄሮ የተጀመረው የውያኔ ግባተ መሬት ያኔውኑ ስለሚጠናቀቅ ዛሬ በእርሱና በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተቃጣው የወያኔ ሲራ ባላጋጠመው ነበር፡፡ 
-
"የኦሮሞ ህዝብ ሆይ! አሁን አንድ ነገር መገንዘብና ማስተዋል ግድ ይለናል፡፡ ኦህዴድ ህዝባችንን ከወያኔ ጥቃት ማዳን ይቅርና እራሱንም ሊያድን አይችልም፡፡ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ለኦሮሞ ህዝብ መብት መከበር ታግለው የሚያታግሉ ግንባር ቀደም ወገኖቻችን በየቀኑ በወያኔ ነጭ ለባሾች እየታፈኑና እየተገደሉ ይገኛሉ። የአብዴ ኢሌ ልዩ ፖሊሶች አረርም ህዝባችን ላይ መዝነቡን ቀጥሎበታል። መታገሳችንና ለኦህዴድ ጊዜ መስጠታችን ከተገቢው በላይ ሄዷል። ትዕግስታችን ለወያኔ ሴራ መልሶ መጠናከር ዕድል ሰጥቷል። የህዝባችንንና የኦህዴድንም ህልውና ለበለጠ አደጋ የሚያጋልጥበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በኦሮሞና በኦሮሚያ የወደፊት ህልውና ላይ ከፍተኛ አደጋ አንዣብቧል። ከእኛ በስተቀር ለህዝባችን ጩሀት አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጥ ሌላ አካል በፍጹም እንደሌለ ለማረጋገጥ ከዚህ በላይ መቆየት አጉል የዋህነት መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል። በወያኔ ጁንታ ለተከፈተብን መጠነ ሰፊ ወረራ ብቸኛው መፍትሔ ትግላችንን ማፋፋም ብቻ የመሆኑን ሀቅ ለማመን በየቀኑ እየደረሰብን ካለው ግልጽ ወረራ፣ ዘረፋና ግድያ በላይ ሌላ ማስረጃ መጠበቅ አያስፈልገንም። ሰሞኑን የሰማነው የወያኔ መግለጫም ይህንኑን የሚያረጋግጥ ጉልህ ማስረጃ ነው፡፡
-
"ስለዚህ ካንዣበበብን ከፍተኛ አደጋ የህዝባችንና የአገራችንን ህልውና ለማዳን በመላው ኦሮሚያ በአንድነት ተነስተን ትግላችንን የምናፋፍምበት ወሳኝ ጊዜ አሁን መሆኑን አስተውለን ለህዝባችን ህልውና፣ ነጻነትና ሙሉ መብት መከበር እንነሳ። ሞትና ሽንፈት ለወያኔ! ድል ለኦሮሞ ህዝብ!"

By: Abbaa Daraar
07/10/2010.

 

                                                              Copyright ©2008 GPO/OPC Allrights Reserved