Gumii Paarlaamaa Oromoo (GPO)

Oromo Parliamentarians Council (OPC)

 

Baga Nagaan Dhuftan!Welcome to Oromo parliamentarians council!

 

 

 

 

 

 

 

 

 

              New Page 2 home                         

 ይድረስ ለፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ

ሟቾችም እኛው፣ ገዳዮችም እኛው፣ መስካሪዎች እኛው፣ ፈራጆችም እኛው - ማን ይቅርታ ይጠይቅ?

(ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)

Email: ahayder2000@gmail.com

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የተባሉምሁር ባለፈው ሰሞንእርቅና ሰላም፤ የህይወት ቅመም በሚል ርዕስ በተለያዩ ድረ-ገፆች ያሰራጩት መዘዘኛ ጽሑፍ ነው፡፡ የፕሮፌሰሩ የጽሑፍ ርእስ አሳሳች ነው፡፡እርቅና ሰላም፤ የህይወት ቅመም የሚለውን ርእስ ከስሩ ካለው የደስ ደስ ያለው የአዛውንት ፎቶግራፍ ጋር የሚያይ ሰው፤ በሕዝቦች መካከል ጦርነት የሚቀሰቅስ መልእክት ይኖረዋል ብሎ ሊጠረጥር አይችልም፡፡

ይህንን መዘዘኛ ጽሑፍ ካነበብኩ በኋላ ቀድሞ የመጣልኝ ጥያቄእኒህ ሰው ማን ናቸው?’ የሚል ነው፡፡ ስለ ጸሐፊው ማንነት ሌሎች ሰዎችን ከመጠየቄ በፊት ግን እንደገና ወደ ጽሑፉ ተመለስኩ፡፡ በስተመጨረሻ አካባቢየአባ ባህርይ ድርሰቶች፣ ኦሮሞዎችን ከሚመለከቱ ሌሎች ሰነዶች ጋራ የሚል መጽሐፍ ማዘጋጀታቸውን አነበብኩ፡፡ ያንን መጽሐፍ ከአስር ዓመታት በፊት ወንድሜ ሙሼ ሰሙ አምጥቶልኝ ማንበቤን አስታወስኩ፡፡ ወዲያውኑምእሳቸውማ ምንም ነገር ከማድረግ የማይመለሱ ልማደኛ ናቸው የሚል ግምቴን በልቤ ይዤ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ማውጠንጠን ያዝኩ፡፡

መቼም እንዲህ ዓይነት አሳሳች ነገርን አይቶ እንዳላዬ፤ ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ በአርምሞ ማለፍ በታሪክ ፊት ያስጠይቃል፡፡ የአባ ባህርይን መጽሐፍ ትርጉም ባነበብኩበት ወቅት፤ መጽሐፉ በታሪክ ማጣቀሻነቱ ያለው ፋይዳ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ታትሞ ገበያ ላይ የዋለበት ወቅት (1996 . ይመስለኛል) ግን የምርጫ ዋዜማ ስለነበር ጥሩ አልነበረም፡፡ በምርጫ ቅስቀሳ ናላው የዞረ ሕብረተሰብ በስሜት ተነሳስቶ ምን እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል በመገመት በመጽሐፉ ትርጉም ሳይሆን፤ ለትርጉሙ ማብራሪያ ተብለው የቀረቡት ሃሳቦች የፈጠሩብኝን ስሜት ዋጥ አድርጌ ማለፌን አስታውሳለሁ፡፡ አሁን ግን ዝም እንድል ግድ የሚለኝ ሁኔታ ባለመኖሩ እነሆ ብዕሬን አነሳሁ፡፡

ፕሮፌሰር ጌታቸው የቋንቋ ምሁር መሆናቸውን ሰምቻለሁ፡፡ የሀገሪቱ ፖለቲካ እየተበላሸ እንዲሄድና እውነተኛ የፖለቲካ መሪዎች ተጠናክረው ወጥተው ፖለቲካውን በመምራት ለውጤት ሊያበቁት ያልቻሉት፤ የቋንቋውም፣ የጂኦግራፊውም፣ የባዮሎጂውም፣ ምሁር በሀገሪቱ ፖለቲካ እጁን እስከ ትከሻው ድረስ ነክሮ ካላማሰልኩ በማለቱ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ በርግጥ አንድ ሰው የፖለቲካ ሳይንስ ስለተማረ ፖለቲካ ያውቃል ማለት አደለም፡፡ ከፖለቲካ ሳይንስ ውጪ የተማረ ሰው ፖለቲካ አያውቅም፣ በሀገሩ ፖለቲካ አያገባውም ማለትም አደለም፡፡

ፖለቲካ በባህሪው ሳይንስም ጥበብም ነው፡፡ (Politics is an art and a science) ሳይንሱን በትምህርት፣ ጥበቡን በተፈጥሮ ማግኘት ይቻላል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ቁምነገሩ ባዮሎጂ ወይም ምህንድስና አሊያም ሕግ መማሩ አደለም፡፡ ቁምነገሩ ሳይንስንና ጥበብን ከተፈጥሮ

የማገናዘብ ክህሎት ጋር አጣምሮ በእውቀትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ መንገድ መከተሉ ነው፡፡

የፕሮፌሰር ጌታቸውን ጽሑፍ እንዳነበብኩ ለአንድ የታሪክ ዶክተር የአክስቴ ልጅ ደወልኩለት፡፡ ጽሑፉን እንዳየው ገልፆልኝ፣የአንድ ግለሰብ አስተያየት ነው፡፡ ይቅርታ ጠይቁ የተባሉት አንጠይቅም ብለው ዝም ሲሉ ነገሩ እዚያ ላይ ይቆማል፡፡ ፀጉር መንጨት አያስፈልግም ነበር ያለኝ፡፡ በርካታ ታላላቅ የዓለም ጦርነቶች በሁለት ግለሰቦች ጠብ የተጀመሩበት አጋጣሚ እንዳለ ታሪክ ይነግረናል፡፡ እናም የፕሮፌሰር ጌታቸውን ጽሑፍ መልእክት የአንድ ግለሰብ ተራ አስተያየት አድርጌ ለመውሰድ ይቸግረኛል፡፡ ሩቅ ሳንሄድ እዚያው የፕሮፌሰሩ ጽሑፍ ላይ እንዳየሁት እርሳቸው የጀመሩትንሀገርን የማበጣበጥ ዓላማ ከግብ ለማድረስ ከመሰሎቻቸው ጋር በመሆን www.ethiopiawin.net/ እና www.ethiopiawin.org/ የሚል ዌብ ሳይትና የበጎ አድራጎት ማህበር አቋቁመው የተደራጀ ሥራ እየሰሩ መሆኑን ነግረውናል፡፡

እኔ እንደሚገባኝ በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ በተንኮል የተራቀቁ፣ አእምሯቸው መጥፎ ነገር በማቀነባበር የተካነ፣ ያንንም ካላደረጉ ሰላም የሚያገኙ የማይመስላቸውሙላቃ ሰዎች አይጠፉም፡፡ እነዚህ ሰዎች ከግል እንቅስቃሴ አልፈው ተሰባስበውእብደታቸውን የሚያስፋፉበት ማህበር ካቋቋሙ አደጋው የከፋ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ኢህአዴግ እንዲህ ያለውንየሽብር ማህበር አይቶ እንዳላዬ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ ያልፍና፤ በኢ-ሜይል ዜና አቀብለሃል፣ መድረክ ላይ የሽብር ንግግር ተናግረሃል፣ ምናምን እያለ ሰዎችን በአሸባሪነት ፈርጆ ያስራል፡፡ ለኔ ሽብር ማለት እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸው ዓይነት ብሔርን ከብሔር፣ ሃይናኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጭ አደገኛ ጽሑፍ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ አንድን መምህር ወሬ አቀብለሃል በሚል ሰበብበአሸባሪነት አስሮ ጀግናም ጋዜጠኛም ማድረግ ትርጉሙ አይገባኝም፡፡ (በነገራችን ላይ ኢህአዴግ በሰራው ስህተት በርካታ ሰዎች ያን ያህል ስማቸውን የሚያስጠራ ስራ ሳይሰሩ በመታሰራቸው ብቻ ተወድሰዋል፣ ተሞግሰዋል፣ዓለም አቀፍ ሽልማት ጭምር ተሸልመዋል ሲባል ሰምተናል፡፡ የታሰረ ሁሉ የተበደለ፣ የታሰረ ሁሉ ጀግና ነው የሚል ስነ-ልቦና አይጣል ነው!)

ሽብር ዓለም አቀፍ ችግር እስከሆነ ድረስ ማንም ሰው የትም ቦታ ሆኖ ቢሰራው ወይም ቢያቀነባብረው ወይም ቢያውጠነጥነው ባለበት ሐገር የፀረ-ሽብር ሕግ መሰረት ተጠያቂ ከመሆን አያመልጥም፡፡ ኢህአዴግ ይህንን ቢያደርግ በምድርም በሰማይም ይጸድቅ ነበር፡፡ ግና ምን ያደርጋል! (ሃያ ሁለት ዓመት ሀገር ቢመራም) መካሪ የሌለው ንጉስ ሆነብን!!! ለመንደርደሪያ ይሆነኝ ዘንድ ይህንን ካልኩ በኋላ የፕሮፌሰር ጌታቸውን ጽሑፍ እየጠቀስኩግብረ ሽበራ መሆኑን ወደ ማሳየቱ ላምራ፡፡

ፕሮፌሰር ጌታቸው መዘዘኛ ጽሑፋቸውን የሚጀምሩት በመቆጨት ነው፡፡ እንዲህ ይላሉ፤እውነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ተመጽዋች ሆኖ የቀረው የማሰብ ችሎታው ዝቅተኛ ሆኖ ነው? አይመስለኝም ይላሉ፡፡ ይህ አባባል ከጽሑፉ ርእስ ጋር ዝምድና ያለው ስለመሆኑ ግር ቢለኝም ሃሳቡ እንደ ሃሳብ ችግር አልነበረውም፡፡ ትንሽ ዝቅ ብለው ግን የድህነታችን መንስዔመሬት በወያኔ ቁጥጥር ስር መሆኑና አገሪቱ በክልል በመከፋፈሏ ዜጎች ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው ሄደው በሰፊው ማረስ ስለማይችሉ…” መሆኑን ፕሮፌሰር ሥዩም ገላዬን በዋቢነት ጠቅሰው ይነግሩናል፡፡

በምኒልክ ዘመን የደነቆረ ዕድሜልኩን ምኒልክ ይሙት ይላል እንዲሉ፤ ሃያ እና ሰላሳ ዓመታት ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖር ሰው አሁን በሀገሪቱ ስላለው ተጨባጭ ሁኔታ በቅርብ ሳያይ ከርቀት ሆኖ በሚሰማው መረጃ ላይ ተመስርቶ ድምዳሜ ላይ መድረስ ትልቅ ድፍረት

ብቻ ሳይሆን ሕዝብን አያውቅም ብሎ መናቅ ሆኖ ነው የሚታየኝ፡፡ወያኔ ስልጣን ላይ የወጣው የዛሬ ሃያ ሁለት ዓመት፤ ድህነቱ አብሮን የኖረውለሦስት ሺህ ዘመናት! የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና፤ ፕሮፌሰር ጌታቸው ራሳቸውወያኔን አሽቀንጥረው ጥለው ስልጣን ቢይዙ (ተዓምር ካልተፈጠረ በስተቀር) ለዘመናት የተከመረ ድህነት በአጭር ጊዜ የሚለቀን አይመስለኝም፡፡

ከጽሑፌ ርእስ ስለሚያስወጣኝ ነው እንጂ የድህነት መንስዔ ተብለው በተጠቀሱት ሁለት ነጥቦች ዙሪያም ላይ ቢሆን የተለየ የራሴ እይታ ነበረኝ፡፡ እሱን እንተወውና ወደ ሌላው የፕሮፌሰር ጌታቸው ሃሳብ እናምራ፡፡ የአክሱምን ስልጣኔ ዮዲት ጉዲት፣ የአምሐራን ስልጣኔ ግራኝ አህመድእሳት የለቀቁበት መሆኑን ከገለጹ በኋላ፤እነዚህ ሁለት ስልጣኔዎች በመጥፋታቸው ባለንበት ቆመን ቀረን ይላሉ፡፡

የአክሱሙን የሩቁን ዘመን ትተን ፕሮፌሰር ጌታቸው እንደሚሉት የግራኝንየጥፋት ዘመን እንይ፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመው የዛሬ አምስት መቶ ዓመት ገደማ ነው፡፡ ዛሬ ዮዲትም ግራኝም የሉም፡፡ ታዲያ ለምን ቁመን ቀረን? የሙት መንፈሳቸው ቅዠት ለቀቀብን? ፕሮፌሰር አህያውን ትተን ዳውላውን አንፈልግ፡፡ የድህነታችን ዋነኛ ምክንያት ስንፍናችን ነው! የተፈራረቁብን ስርዓቶች ያደረሱት በደልም ቢሆን ሁለተኛ እንጂ ቀዳሚ ምክንያት ሆኖ አይታየኝም - በበኩሌ፡፡ ኢትዮጵያውያን ስንባል ፈሪዎች ነን! - በራሳችን ላይ ሂስ የማውረድ፣ ራሳችንን የመተቸት፣ ፍርሃታችን ልክ የለውም፡፡ አሁንም ዳርዳሩን አንሂድ! ሰነፎች ነን! ደካሞች ነን! ድህነት በላያችን ላይ ጎጆውን ቀልሶራፕ ሲጨፍርብንእሱ ያመጣውን እሱ እስኪመልሰው…” ብለን ተከናንበን ለጥ አልን፡፡ ዓለም ጥሎን ፈረጠጠ፡፡ እኛበአክሱም ዘመን፣ በላሊበላ፣ በፋሲል፣…” እያልን ታሪክ ስናመነዥክ እና ተረት ተረት እያወራን ስንቆዝም፣ ዓለም በስልጣኔ ገስግሷል፡፡ ልቋል! አምልጧል!!!

ፕሮፌሰር ይህንንም ብለው ቢያቆሙ መልካም ነበር፡፡ ግን ይቀጥላሉ! “ኦሮምኛ የሚናገሩ ጎሣዎች የእስላሞቹ አመፅ በተገታ ማግስት ፈልሰው፣ ከእስላሞቹ የተረፈውን የስልጣኔ ምልክት ጠራረጉት ጋዳ በሚሉት [ገዳ ማለታቸው ነው] ሁሉን ለጦርነት በሚያሰልፍ የማፊያ ስርዓት በውትድርና ተደራጅተው፤ በግብርና፣ በንግድ፣ በድብትርና የሚተዳደረውን ሰላማዊ ሕዝብ አረዱት፣ ንብረቱን አወደሙት፡፡ በእርሻው፣ በሰብሉ ላይ ከብታቸውን አሰማሩበት፡፡ በባህላቸው መሰረት ክርስቲያን ያልገደለ በቅማል ይሰቃያል እንጂ ራሱን አይላጭም ነበር፡፡ ሸዋን፣ ጎንደርን፣ ጎጃምን፣ አምሀራን (የዛሬውን ወሎ) ደመሰሷቸው…” በማለት የተረት ተረት ትረካቸውን ይቀጥላሉ፡፡

ፕሮፌሰር ጌታቸው ከላይ የተጠቀሰውን ትረካ ሲያቀርቡ፤ 16ኛው ክፍለ ዘመን እዚያው ቦታው ላይ ቁጭ ብለው ሂደቱን በዓይናቸው በብረቱ ያዩ ይመስላሉ፡፡ እንዲህ ያለውን ትረካ ነው የታሪክ ምሁራንየደብተራ ታሪክ የሚል ስያሜ የሰጡት፡፡ (ፕሮፌሰር ጌታቸው ግን ደብተራነት ተመራማሪነት መሆኑን በዚሁ ጽሁፋቸው ላይ ገልጻዋል - ድንቄም ምርምር!) ራስ አለመላጨትን በተመለከተ መቼም በዚያ ዘመን (የዛሬ 500 ዓመት ገደማ) ቀርቶ እነ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሕፃን በነበሩበት ዘመንም ቢሆን ከከተሞች አልፎ በየገጠሩፌላ ምላጭ እንደልብ የሚገኝ አይመስለኝምና ነገሩን ወዳልሆነ አቅጣጫ ወስደው፣ መያያዝ የማይችለውን አጨማደው ለማያያዝ ባይሞክሩ መልካም ነው፡፡

የፀጉር መላጨት ጉዳይ ከተነሳ አይቀር የማውቀውን ልንገርዎ ፕሮፌሶሬ! እኔ 1960ዎቹ መጀመሪያ፣ በአንዲት የገጠር መንደር ነው የተወለድኩት፡፡ ያኔ አንዱ የመንደራችን ሰው ምላጭ ከገዛ፣ ምላጩ ዶልዱሞ በቃኝ እስኪል ድረስ የጎረቤት ልጆች በሙሉ እንላጭበት ነበር፡፡

ሌላ የሰፈሩ አባወራ ሌላ ምላጭ እስኪገዛ ድረስ ያልተላጩት የመንደራችን ልጆች የተባይ መጫወቻ ሆነው ይከርሙ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ እናም፤ የኦሮሞዎችን የዛሬ አምስት መቶ ዓመት ፀጉር አለመላጨት (እሱም ጥላቻ ከፈጠረው ተረትነት ያለፈ ሆኖ አይታየኝም) ይተውትና ፕሮፌሰር ጌታቸው ሕፃን በነበሩበት ዘመን ፀጉራቸውን እየተላጩ ስለማደጋቸው የራሳቸውን ታሪክ ይንገሩን! በምን ዓይነት ምላጭ ይጠቀሙ እንደነበር ጭምር ያውጉን! - መቼምበጂሌት እየተላጨሁ ነው ያደግኩት እንደማይሉን ተስፋ አደርጋለሁ!

እንደኔ እንደኔ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን የተላበሰ ሰውክርስቲያን ያልገደለ በቅማል ይሰቃያል ምናምን እያለ ማስረጃ የማይቀርብበት እላፊ ንግግር አይናገርም ወይም አይጽፍም፡፡ ፊውዳላዊ አስተሳሰብ አንድ ጊዜ በደም በአጥንታችን ውስጥ ከገባ የፈለገውን ያህል በእውቀት ብንጥለቀለቅ፣ ያሻውን ያህል በጥበብ ብንራቀቅ፣ ከሰለጠኑ ሕዝቦች ጋር ለዓመታት ብንዘልቅ፣ ሊለቀን አይችልም፡፡ የንግግራችንም ሆነ የጽሑፋችን ቃና ያንኑ የኖርንበትን ዘመን ነው የሚመስለው፡፡

ፕሮፌሰሩን፤ 16ኛው ክፍለ ዘመን የተደረገው ድርጊት ያንገበገባቸውን ያህል የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ አፄ ዮሐንስዝቅ ብለህ ባቱን ከፍ ብለህ አንገቱን እያልክ አጥምቅልኝ (ክርስቲያን አድርግልኝ) ማለታቸውንም ሆነ፤ ነፍጠኛው የአፄ ምኒልክ ጦር አካል እየቆረጠ፣ ንብረት እየዘረፈ፣ ነባር ሕዝቦችን ከመሬታቸው መንቀሉን በተመለከተ ምንም አይሉም፡፡ ይሄ በእስላሞች፣ በኦሮሞዎች እና በደቡቦች ላይ የደረሰ ግፍ በመሆኑ ለእርሳቸው ምንም አደለም፡፡ ምናልባትም፤ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ፕሮፌሰሩ መከራ እንዲወርድባቸው የሚፈልጓቸው በመሆኑ፣ በእነርሱ ላይ የደረሰውን ግፍ ማየት አልፈለጉ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያን እወዳለሁ የሚል ሰው እንዲህ ያለ የለየት ወገንተኛ ጽሑፍ ይዞ ሕዝብ ፊት ሲቀርብ ግርርርም አይልም? (ለነገሩ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ያለ ሁሉ ኢትዮጵያን ይወዳል ማለት አደለም) እንደ ምሁር ማድረግ የነበረባቸው፤ ከተቹ አይቀር በቅርብም በሩቅም ዘመን የጠፋውን ጥፋት መተቸት ነው፡፡ ካለበለዚያአጠፉ ብለው ከሚተቿቸውና ከሚወቅሷቸው ሰዎች በምን ይሻላሉ?

ፕሮፌሰሩ እዚህም ላይ ቢያቆሙ ደግ ነበር፡፡ ግን ይቀጥላሉ፡፡እስላሞቹ የክርስቲያኖቹን ስልጣኔ አጥፍተው በራሳቸው ሥነ-ጽሑፍ ሊተኩት አስበው ነበር፡፡ ኦሮምኛ ተናጋሪዎቹ ግን እረኞች ስለነበሩ ስልጣኔን በሥነ-ጽሑፋዊ ስልጣኔ የመተካት ግዴታ አልነበራቸውም በማለትየስልጣኔ ባለቤት የሆኑትን ሕዝቦች የደመሰሱትእረኞች መሆናቸውን ይነግሩናል፡፡ እንዲያው ለነገሩ በየት አገር ነውእረኛ” “የሰለጠኑ ሕዝቦችን የሚደመስሰው ፕሮፌሶሬ? በየትኛው አቅም? ካልሆነ እነዚያእረኛ የተባሉት እውነትምእረኛ አልነበሩም ማለት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የሆነ ቦታ ላይ የተዛባ ታሪክ መኖሩን የሚያመላክት ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ያለ ከተረትነት አልፎ በራሱ ሊቆም የማይችልና እርስ በርሱ የሚጣረስ ሃሳብ በማቅረብ ትዝብት ላይ ባይወድቁ ምናለ ጃል?!

ፕሮፌሰር ጌታቸው በተረት ተረት የታሪክ ሰረገላ የሚያደርጉትን ጉዞ በመቀጠል ወደ ጽሑፋቸው መቋጫ የሚወስዳቸውን ሃሳብ እንዲህ በማለት ይቀጥላሉዛሬ ለራስ ጎበና ዳጬ ያልሆነ፣ ያልተደረገ የአረመኔነት ታሪክ እየተፈጠረለት መሆኑን ከገለጹ በኋላ፤ውሸት ታሪክ አይሆንም በማለት በጎበና ዳጬ ፊት አውራሪነት የደረሰ ጥፋት እንደሌለ ሽምጥጥ አድርገው ይክዳሉ፡፡ እዚህ ላይ፤ ፕሮፌሰር ለራስ ጎበና ዳጬ ያሳዩት ተቆርቋሪነትካንጀት ነው ካንገት?” የሚል ጥያቄ ጣል አድርጌ ማለፍን መረጥኩ፡፡

ፕሮፌሰር ጌታቸው ወደ ጽሑፋቸው መቋጫ በመንደርደርም ሦስትየእርቅና ሰላም ሳይሆንየግብረ ሽበራ ውሳኔዎችን እንዲህ በማለት ያቀርባሉ፡፡አንደኛ እርምጃ፤ ከላይ እንደገለጽኩት

እስላሞችና ኦሮምኛ ተናጋሪ ጎሣዎች ኢትዮጵያን እንዴት እንዳቆረቆዟት ታሪኩ እንዳይፋቅ ሆኖ ተጽፏል፡፡ የሚፈለገው ግን እርቅና ሰላም ነው፡፡ ለዚህም መሆን ያለበት የመጀመሪያው እርምጃ አባቶቻችንን እንወክላለን የሚሉ እስላሞችና ኦሮሞዎች በኢትዮጵያ ላይ ላደረሱት ጥፋት የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ይጠይቁ፡፡

ሁለተኛ እርምጃ፤ አፄ ምኒልክና ራስ ጎበና ዳጬ የተበታተኑትንና እርስ በርሳቸው የሚባሉትን ኦሮምኛ ተናጋሪዎች አንድ ያደረጉበትን ቀን ኦሮሞኛ ተናጋሪዎች በጬፌአቸው ወስነው በየዓመቱ ማክበር አለባቸው፡፡ ሦስተኛው እርምጃ ማንን እንደሚመለከት ግልጽ ባይሆንምአስተሳሰባቸውን Primitive ወደ Modern ዘመን አስተሳሰብ መቀየር አለባቸው የሚል ቀጭን ትእዛዝ በማስተላለፍ ጽሑፋቸውን ይቋጫሉ፡፡

ውድ አንባብያን! እዚህ ድረስ በንባብ ተከትላችሁኝ ከመጣችሁ የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌእርቅና ሰላም፤ የህይወት ቅመም የሚል ርእስና የጽሑፋቸው ይዘት ሰላምን የሚሰብክ፣ እርቅን የሚያወርድ ሳይሆን፤ ጠብና ቁርሾን የሚቀሰቅስ፣ ጦርነትን የሚጭርግብረ ሽበራ መሆኑን እንደምትገነዘቡ አምናለሁ፡፡ በበኩሌ እንዲህ ያለ ተንኳሽ ሃሳብ ከአንድ ጎምቱ ሽማግሌ፣ እድሜ ልኩን በጥናትና ምርምር ካሳለፈ ፕሮፌሰር ቀርቶ ከአንድወፈፌ ዜጋ መሰንዘር የሚገባው ሆኖ አይታየኝም፡፡

የሀገራችን ታሪክ ውስብስብ ነው፡፡ በዚያ ላይ በደም የቀላ ነው፡፡ እናም በበሰሉ የታሪክ ሊቃውንት፣ ገለልተኛነትን በጠበቀ ሁኔታ፣ በአስተማማኝ ሰነድና መረጃ ላይ ተመርኩዞ ቢጠና ከጥሩውም ከመጥፎውም ሁሉም ወገን ይማርበታል፡፡ ማንበብና መጻፍ ስለቻልን ብቻ ሁላችንም ከሙያችን ውጪ እንዳሻን እጃችንን እስከ ብብታችን ድረስ እያስገባን የምናማስለው ከሆነ ግን ውጤቱ ድስቱን መሰባበር ይሆናል፡፡ በዚህ ደግሞ ማናችንም ተጠቃሚ፣ ማናችንም አትራፊ አንሆንም፡፡

እኔ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የታሪክ ምሁር አደለሁም፡፡ ማኔጅመንት፣ ፖለቲካል ሳይንስና ኢኮኖሚክስ ነው የተማርኩት፡፡ በመጠኑም የህግና የሶስዮሎጂ ኮርሶች ወስጃለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን ስለሀገሬ ታሪክ የታሪክ ምሁራን የጻፉትን አላነበብኩም ማለት አደለም፡፡ አቅሜ በፈቀደ ሁሌም ለማንበብ እጥራለሁ፡፡ በታሪክ ምሁርነት ራሴን ሞሽሬ ግን አልንጠራራም ለማለት ነው፡፡ በኔ ግንዛቤ ሀገራችን የተፈጠረቺው እውስጧ ባለነው ዜጎቿ ጠብና ፍቅር፣ ግጭትና መገዳደል፣ መገንባትና ማፍረስ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ይህ ለምን ሆነ ማለት አንችልም፡፡ ብንልም አንዴ ሆኗልና ልንለውጠው አይቻለንም፡፡

ፕሮፌሰር ጌታቸው እንዳሉት ዮዲት ጉዲት (ትክክለኛ ስሟ ግን ባኑኤል ሐይሙያ ነው ይባላል) በዘመኗ አልገብርም ያሏትን በጉልበቷ አስገብራለች፡፡ በሂደቱም ብዙ ብዙ ጥፋት ማድረሷ እርግጥ ነው፡፡ ዛሬ፣ በሦስተኛው ሚሊኒየም፣ 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሆነን ይሄን ለምን አደረገች? ወይም እነዚያስ ለምን ፀጥ ለጥ ብለው አልገበሩላትም? የሚል ጥያቄ አንስተን ለመከራከር መሞከር ጉንጭን ከማልፋት የዘለለ ትርጉምም ፋይዳም አይኖረውም ባይ ነኝ፡፡ ትልቁ ቁም ነገር ከዚህ ጥፋት ትምህርት ወስዶ ተመሳሳይ ስህተት ከመስራት መቆጠቡ ላይ ነው፡፡

ኢማም አህመድ ኢብን ኢብራሂም አልጋዚ (ግራኝ) በዘመኑ የዛሬዋን ኢትዮጵያ በመፍጠሩ ሂደት የድርሻውን ተወጥቷል፡፡ እንዲያውም ከግራኝ በፊት ያን ያህል ሰፊ ግዛት ያስተዳደረ የኢትዮጵያ መሪ ስለመኖሩ በእርግጠኛነት መናገር የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ለዚህም ነው አንዳንድ ጊዜኢትዮጵያን የፈጠሯት ግራኝ እና ኦሮሞዎች ናቸው የሚል ሃሳብ መሰንዘር

የሚቃጣኝ፡፡ ስለሆነም፤ በውለታ ቢስነትየግራኝ አህመድ ወረራ ምናምን በማለት ይህንን ሀቅ ማጥፋት ቀርቶ ማደብዘዝ አይቻልም፡፡ ኦሮሞዎችም እንዲሁ ከግራኝ የተረፉ ተግባራትን በማከናወን (በተለይም ወደ ደቡብ እና ምዕራብ ኢትዮጵያ ግዛታቸውን በማስፋፋት) ኢትዮጵያን የመፍጠር ታሪካዊ ድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡የማፊያ ስርዓት፣ እረኞች፣ ፀጉራቸውን አይላጩም፣ የኦሮሞ ፍልሰት፣…” የሚሉ ተቀጽላዎችን በመደርደር ሀቁን መቅበር አይቻልም፡፡

በእነዚህ ሁሉ ሂደቶች የሰው ነፍስ ጠፍቷል፡፡ ሀብት፣ ንብረት ወድሟል፡፡ ቅርስ ተቃጥሏል፡፡ ብዙ ብዙ ጥፋት ተፈጽሟል፡፡ ይህ ሁሉ መስዋእትነት ግን ዛሬ ኢትዮጵያ የምንላትን ሀገር አስገኝቶልናል፡፡ ያለ መስዋእትነት ሀገር ቀርቶ የጓሮ መሬት ማግኘት አይቻልም፡፡ ዛሬ አድገዋል፣ ሰልጥነዋል፣ በልጽገዋል የሚባሉት ሀገሮችም ቢሆኑ የተፈጠሩት ከእኛ በባሰ ሕይወትና ንብረት ገብረው ነው፡፡ የአሜሪካውያንን 13 ሚሊዮን ቀይ ሕንዶች የእልቂት ታሪክ ጠቅሶ ማለፍ ብቻ በቂ ይመስለኛል፡፡

አፄ ቴዎድሮስም፣ አፄ ዮሐንስም፣ አፄ ምኒልክም፣ በዘመናቸው ብዙ ብዙ ጥፋቶችን ሰርተዋል፡፡ የከፋው ንጉስ ጋኪ ሲርኮ፣ የወላይታው ንጉስ ጦና፣ የአፋሩ፣ የሀረሪው፣ የወለጋው፣ የቤንሻንጉሉ፣ ጥፋት አልሰሩም፣ ሰው አልገደሉም፣ ሕዝብ አላማረሩም ብለን መመስከር የምንችል አይመስለኝም፡፡ የመጠን ማነስና መብለጥ ካልሆነ በስተቀር አንድም ከደሙ ንፁህ የሆነ የኢትዮጵያ መሪ፣ ሀገር አስተዳዳሪ የሚገኝ አይመስለኝም፡፡ ታመው ለታከሙበት ብር ወይም ወርቅ አሊያም እንስሳት ካልሆነም ቡና ወይም አሞሌ ጨው ሳይሆንባሪያ ይከፍሉ የነበሩ የኢትዮጵያ ንጉሶች መኖራቸው የታሪክ ሰሌዳ ላይ ተጽፏል፡፡ እነዚህ ሕዝብ የከፈላቸው መስዋእትነቶች ግን ኢትዮጵያችንን አስገኝቶልናል፡፡

ይኸን ሁሉ መስዋእትነት አረም ጭነንበት ዛሬ በያቅጣጫው እየተነሳን እከሌ እንዲህ አድርጎ፣ እንቶኔ እንትን ቆርጦ፣ ሀገር አቆርቁዞ፣ ምናምን እያልን በይቅርታጠይቅ’ ‘አትጠይቅ አታካሮ ጊዜና ጉልበት ማባከኑ ከአያቶቻችን ስህተት ያልተማርንና ከእነርሱም የማንሻል ቂሎች መሆናችንን የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፤ ዛሬ መሰራት ያለበትን ሥራ ባለመስራታችን ለልጆቻችንና ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ መከራ እየከመርን መሆኑን የሚያመላክት ይመስለኛል፡፡

ባለፈው ሰሞን በፕሮፌሰር ጌታቸው ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ወገኖች ጎላ ብለው ከተነሱት ሀገራዊ ጉዳዮች አንዱ የሀውልት መሰራትና መፍረስ ጉዳይ ነበር፡፡ እንደኔ እንደኔ ሀውልት የመልካም ሥራ ማስታወሻ ብቻ አደለም፡፡ የመጥፎ ተግባራት መዘከሪያም ነው፡፡ ባይሆን ኖሮ የስድስት ኪሎው የሰማእታት መታሰቢያ ሀውልት በርካታ ገንዘብ ተከስክሶበት የከተማችን ሁነኛ ስፍራ ላይ አይገተርም ነበር፡፡ በጥሩውም በመጥፎውም እያነሳን የምናወድሳቸውና የምንወቅሳቸው ሁሉ ሀውልት ቢቆምላቸው መጪው ትውልድ ከድክመቱም ከጥንካሬውም ይማርበታል፡፡

የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ በአካፓ እና በአውሮፓ ሕብረት የፓርላማ ጉባዔ (ACP-EU-JPA) ላይ ለመሳተፍ ወደ ኦስትሪያ ቬና ሄጄ ነበር፡፡ ከተማዋን ስንጎበኝ የንግስት ማሪያ ትሬዛ ሀውልት ደረስን፡፡ አስጎብኛችን ስለ ሀውልቱ በርካታ ነገሮችን ከነገረን በኋላ፤ዛሬ እዚህ ኦስትሪያ ውስጥ ስትዘዋወሩ ያገኛችሁትን ሕፃን ማሪያ ትሬዛ ማን ናት ብላችሁ ብትጠይቁት፣ማሪያ ትሬዛ 16 ልጆች ነበሯት፡፡ ግን ሁሉም /ቤት አልሄዱም ነበር ይላችኋል ማለቱን አስታውሳለሁ፡፡ ማሪያ ትሬዛ የነበረችው 18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይመስለኛል፡፡ ዛሬ በዚህ ዘመን ግን በኦስትሪያ ብቻ ሳይሆን በመላ አውሮጳ ከሁለት ልጅ በላይ አይወለድም፡፡ እነሱም /ቤት ይገባሉ፡፡ በዚህ መልኩ ትውልድን የሚያንጹ ሀውልቶችን መገንባት ተገቢ ስለሆነ ንትርኩን ትተን እንዲህ ዓይነቱን ብናስብ መልካም ነው፡፡

በርካታቤተክርስቲያኖችን በማቃጠሏና አክሱምን በማውደሟ በብዙዎች ዘንድ የምትወቀሰው ዮዲት ጉዲት ያን ሁሉ ጥፋት የፈጸመቺውእስላም/አይሁድ ስለነበረች ነው ከማለት ውጪ በእሷና በእሷ ወገኖች ላይ ቀድሞ ምን እንደተፈጸመ በግልጽ አለመጠቀሱ አስተያየታችንን ሚዛኑን ያሳተው ይመስለኛል፡፡ ከአፈ ታሪክ (ሌጀንድ) እንደሰማነው ዮዲት በአክሱም ቀሳውስት ላይ ያን ሁሉ ግፍ የሰራቺው ሁለቱንም ጡቷን ቆርጠው፣ እንዳትሞት እንዳትድን አድርገው በርሃ ላይ ስለጣሏት ነው ይባላል፡፡ ውድ ፕሮፌሰር! እና ዮዲት ጉዲት የእርስዎ ልጅ ብትሆንና በግፍ ጡቶቿን ቆርጠው ቢጥሏት ምን ይሰማዎታል? እሷም ኢትዮጵያዊት መሆኗን አንርሳ! ጥቃትን ተሸክማ፣ አንገቷን ደፍታ ታሳልፍ ዘንድ በደሟ ውስጥ ያለው የኢትዮጵያዊነት ወኔ በጄ አይላትም! አላላትምም!!! በወቅቱማድረግ ይገባኛል ብላ የምታስበውንና የምታምንበትን አደረገች - በቃ! የእሷን ጥፋት መመዘን ያለብን በዚያው በዘመኑ በነበረው የእውቀትና የግንዛቤ (Level of Consciousness) ደረጃ ነው፡፡ በትውልዶች (Generation) መካከል ምንጊዜም ልዩነት ይኖራል፡፡ በትውልድ መካከል ልዩነት ባይኖር ኖሮ 1950ዎቹ እና 1960ዎቹ የነበሩ ተራማጅ የባላባት ልጆች፤ የወላጆቻቸው መሬት ለጭሰኛ (ለጭቁን አርሶ አደር) እንዲከፋፈልመሬት ላራሹ በማለት አይጮሁም ነበር፡፡

ክቡር ሆይ! ይልቅ ስለዮዲት ጉዲት ሰሞኑን የሰማሁትን ዜና ልንገርዎ! የዮዲት ጉዲት መካነ መቃብር በትግራይ ክልል ውቅሮ አካባቢ መገኘቱንና ፀሐይና ዝናብ ጉዳት እንዳያደርስበት በክልሉ መንግስት አማካይነት ጣሪያ (ሼድ) የተበጀለት መሆኑን በቅርቡ ወደ አካባቢው ደርሶ የመጣ ጓደኛዬ አጫውቶኛል፡፡ ሥፍራው በቅጡ ተደራጅቶ ቱሪስቶች እንዲጎበኙት ቢደረግ፤ የዮዲት ጉዲት መቃብር የሚያስገኘው ገቢ አክሱም አካባቢ እየተደረገ ላለው የታሪክና የቅርስ እንክብካቤና ምርምር በጀት እንዲሆን ማድረግ ይቻል ነበር፡፡

በዚሁ ዓይነት የግራኝ መቃብር፣ (ግን የት ነው?) ግራኝ ወረወራቸው የሚባሉ ድንጋዮች፣ (አንዱን ወሎ ሐይቅ እስጢፋኖስ አጠገብ ተተክሎ አይቼዋለሁ) የግራኝ ፈረስ ኮቴው ያረፈበት ድንጋይ፣ ወዘተ. እንዲፈለጉ ቢደረግ፤ ኦሮሞዎች ኢትዮጵያን በመፍጠሩ ሂደት ባደረጉት እንቅስቃሴ ያከናወኗቸውን ጥሩም ሆነ መጥፎ ተግባራት የሚያዘክሩ ቅርሶች ተፈልገው እንዲሰባሰቡና በቱሪስቶች እንዲጎበኙ ቢደረግ፤ በዚህም የሚገኘው ገቢ በነዚያ ዘመኖች ለጠፋው ጥፋት ማካካሻ የሚሆንጉማ” (የደም ካሳ) ይሆነን ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸው እና እንደ ሌሎችም የጠገገን ቁስል በመነካካት እንዲያመረቅዝ ከማድረግ ይልቅ፤ ቅድመ አያቶቻችንሰሩት የሚባለውን መጥፎውን የታሪካችንን ገጽታ በበጎ ጎኑ ብንጠቀምበት ለሁላችንም ይበጃል የሚል እምነት አለኝ፡፡

በመጨረሻ፤ ለፕሮፌሰር ጌታቸው ለማሳሰብ የምፈልገው አንድ ዓቢይ ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም፤ በየትም ሀገር፣ ሀገርን የመመስረት (Nation Building) ሂደት በጥፋት የተሞላ መሆኑ ይስተዋላል፡፡ የቢስማክንም፣ የጋርባልዲንም፣ ታሪክ ማውሳት ይቻላል፡፡ የዐረቦችን፣ የቱርኮችን፣ የሩቅ ምስራቅ ሕዝቦችን፣ የአፍሪካንም ሆነ የላቲን አሜሪካንን፣ ሕዝቦች ታሪክ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በእኛም ሀገር የታየው የተለየ አይመስለኝም፡፡ ሁሉም መታለፍ የነበረበት ሂደት (Process) በመሆኑ ሀገራችንና ሕዝቧ ክፉውንም ደጉንም አስተናግደውታል፡፡ አዲዮስ! ጦሱን ይዞ ጀሐነም ይውረድ!

አሁን በዚህ ዘመን ያለን ሰዎች በስሜት እየተነሳሳን አንተ ይቅርታ ጠይቅ፣ አንተ እንደዚህ አድርግ ወይም አታድርግ፣ የምንባባል ከሆነ ሂደቱም ሆነ ውጤቱ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር በዓለም ካርታ ላይ እንድትኖር የሚያደርግ አይሆንም፡፡ ስለሆነም፤ ሟቾችም እኛው፣ ገዳዮችም እኛው፣ መስካሪዎች እኛው፣ ፈራጆችም እኛው፣ ይቅርታ ጠያቂዎቹም እኛው፣ ይቅር ባዮቹም

እኛው፣ ነን፡፡ ከደሙ ንፁህ ሆኖ ማንም በማንም ላይ ጣቱን መቀሰር አይችልም ብለን ብናልፈውና ቀጣዩን ስራ ብንሰራ የተሻለ ይሆናል እላለሁ፡፡ ምን ጊዜም ታዛዥዎ

 

                                                              Copyright ©2008 GPO/OPC Allrights Reserved