Gumii Paarlaamaa Oromoo (GPO)

Oromo Parliamentarians Council (OPC)

 

Baga Nagaan Dhuftan!Welcome to Oromo parliamentarians council!

 

 

 

 

 

 

 

 

 

              New Page 2 home                         

 Artist Oromoo-Ethiopia beekama Lama Guyya Degeersa Media fi xiyeefanoo dhabuu hin qabu.

Artistin Oromoo waan ini hama yoonati hojeete fi barumsa ini ijoolee Oromoo dabarsuu qabu utuun lubun jiru irra barachun garidha. Artist Lama Guyya Sabona Oromoo fi gidiira Oromoo kan hubatuu, Oromoon dandeeti isaa akka gudifatuu xiiqi guda kan qabu, yamuu ta'uu seena Arti biyyati keessati bakka isaaf maluu argachuu dhabun isaa Oromoo waan ta'eef ala qabamuu isaatu nutu dhaga'ama. Seena Artii keessati nami waggota hamasi kakaumisa isaan hoji akkasi hojeete seena keessati galamuu qaba ture. Garuu Seena Artisti kana akkuma seena Baaroo Tumsaa, Dr. Haile Fidaa seena hayyulee Oromoo dhokate hafuuf deema. Gummin Paarlamaa Oromoo Nama bareefama kana qoopheese obbo Gazigni Dinkuf galata gudaa qaba seenan Artisti kana dhokachuu hin qabu.  

 አንጋፉውን ሰዓሊ በአድናቆት

                                                                 

አንጋፋው ሰዓሊ ለማ ጉያ

ሰዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ ማዕከሉን ለመጎብኘት ከስኩል ኦፍ አይጎዳ ከአዲስ አበባ ከመጡ ተማሪዎች ጋር

ከገዛኸኝ ድንቁ (ጀርመን)

ሥዕል ከሥነ ጥበብ የፈጠራ ሥራዎች ሙያ ዘርፎች አንዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የካቲት 1993 ዓ᎐ም ባሳተመው ጥልቅ የሥነ ቋንቋ ጥናት የአማርኛ መዝገበ ቃላት ላይ ስዕል ቀጥተኛ ትርጉሙን እንዲህ ሲል ይፈታዋል::

ስዕል ማለት ለዓይን እንዲታይ ተደርጐ በወረቀት፣ በሸራ፣ በግድግዳ ወዘተ ላይ በእርሳስ፣ በብሩሽ፣ በብዕር...የተሰራ፣ የተነደፈ ወይም ከጠጣር ነገር የተቀረጸ የአንድ ነገር ወይም ሃሳብ፣ መልክ፣ ቅርጽ፣ ምስል ነው ይለዋል[1]፡፡

ይህን ከላይ የተገለጸውን የኪነ ጥበብ ዘርፍ ብዙዎች ቢመኙትም በተፈጥሮ የሚታደሉት ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ ሰዓሊ ለመሆን በዘመናዊ ትምህርት ከሚገኝ እውቀት ባሻገር የተፈጥሮን ተሰጥኦnatural gift ) መጐናጸፍ ይጠይቃል፡፡ ይህንንም ተፈጥሮሃዊ ተሰጥኦ ገና ከህጻንነት ዕድሜ ጀምሮ የዝንባሌን አቅጣጫ (directionለይቶ በማወቅ በውስጥ የታመቀውን ረቂቅ ጥበብ በፈጠራ ሙያዊ ሥራዎች ወደ ውጫዊው ዓለም ወጥቶ እንዲታይ ጥረት በማድረግ የዚህ ተፈጥሮሃዊ ጸጋ ( talent ) ባለቤት መሆንን ይሻል፡፡ ይህን ጸጋ ከታደሉት ጥበበኞች መካከል አንዱ አንጋፋው ኢትዮጵያዊ ሰዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ ናቸው ።

ሰዓሊው በቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው አድአ ሊበን ወረዳ ተብሎ በሚጠራው የደሎ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ከገበሬ ቤተሰብ በ 1921 ዓ᎐ም መወለዳቸውን በአንደበታቸው ይገልጻሉ፡፡ ዛሬ የ85 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ አንጋፋ ሰዓሊ ናቸው፡፡

እኚህ ሰዓሊ የስዕል ሥራና ቅርጻ ቅርጽ ጥበብ በውስጣቸው የፈነጠቀው ገና በልጅነታቸው ነበር፡፡ አመድ በጥብጠው በግድግዳ ላይ ልዩ ልዩ የእንሰሳት ስዕሎችን ይሞነጫጭሩ እንደነበርና፣ ጭቃ እያቦኩ ደግሞ የተለያዩ ቅርጻ ቅርጾችን ይሰሩ እንደነበር በትውስታ ያወጋሉ፡፡ ይበልጥ ደግሞ የተፈጥሮ ጸጋ እንዳላቸው ያወቁት ከመሃል ከተማ አባታቸውን ሊጠይቋቸው የሚመጡ ሰዎች በሥራቸው በመደነቅ “ይሄ ልጅ ጐበዝ ነው! ሃሳብ አለው! ት/ቤት ብታስገባው ጥሩ ነው! ···”በሚለው የማበረታቻ ቃል ግፊት (motivation) አባታቸው ወደ ት/ቤት ልከዋቸው ትምህርት እንዲጀምሩ መደረጋቸው ነበር፡፡ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥም ትምህርታቸውን አጠናቀቁ፡፡ በእነዚህ የትምህርት ቆይታ ጊዜያትም የጥልፍና የእጅ ሥራዎችን ተከታተሉ፣ከዚህ በኋላም በናዝሬት የመምህራን ኮሌጅ ገቡ፡፡

ከዚያም በኮሌጁ ውስጥ የአንድ ወር ቆይታ ካደረጉ በኋላ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ መንግስት አየር ኃይል ተቀጥረው በአውሮፕላን መካኒክነት ለሁለት ዓመት የሚሰጠውን ሥልጠና ወሰዱ፡፡ ታዲያ አጼ ኃይለ ሥላሴ አረንጓዴ ባህርን ጐብኝተው በጋራ በሩ ተራራ ሥር ታጅበው ሲመለሱ ተመለከቱ፡

ሰዓሊውም የመጀመሪያ የስዕል ስራቸውን በ1946 ዓ᎐ም “ግርማዊነታቸው ከአረንጓዴ ባህር ሲመለሱ ” በሚል መጠሪያ ሀ ብለው ወደ ጥበብ ዓለም ጉዞሃቸውን ጀመሩ፡፡ በዚሁ ወቅት ለንጉሱ የአውሮፕላን ሞዴል ሠርተው በማቅረባቸውና በስጦታም በማበርከታቸው ንጉሱ በፈጠራ ሥራቸው ተደነቁ፡፡ ከዚያም ለፈጠራ ሙያቸው ማበረታቻ ይሆን ዘንድ ወጣቱ ሰዓሊ ለማ ጉያን በአየር ኃይል የመኮንንነት ኮርስ ዕድል እንዲያገኙ የዕድገት በር ከፈቱላቸው፡፡

በስዕል ሙያ ላይ ያላቸውን ተፈጥሮሂዊ ክህሎት ይበልጥ ለማሳደግ ምቹ ሁኔታን የፈጠረላቸው በመኮንንነት ከተመረቁ በኋላ በወቅቱ አስመራ በነበረው የአየር ኃይል ቤዝ ተልከው ለረጅም ጊዜ ግልጋሎት በዚያ በመስጠታቸው ነበር፡፡ በዚያም ወርቃማ ጊዜያትና ጥሩ አጋጣሚን እንደፈጠረላቸው ይናገራሉ፡፡ ጣሊያናዊ ሰዓሊዎችን ለመተዋወቅና ሥራዎቻቸውንም ለመጎብኘት ዕድሉን አግኝተዋል፡፡ በውስጣቸው ታምቆ የነበረው የፈጠራ ስሜትም በአጋጣሚ ልቆ ወጥቶ በርካታ የስዕል ሥራዎችን ለመስራት ችለዋል። በ1950 እና በ1952 ዓ.ም በአስመራ ከተማ ሁለት የስዕል ኤግዚቢሽኖችንም አሳይተዋል፡፡ በአየር ኃይል ውስጥም በፎቶ ሰክሽንና በህዝብ ግንኙነት መኮንን የሀላፊነት ቦታ ላይ ሆነው አገልግለዋል፡፡

በአስመራ የሥራ ግዳጃቸውን ጨርሰው ወደ ደብረ ዘይት/የአሁኗ ቢሾፍቱ/ ከተማ እንደተመለሱም በከተማዋ ውስጥ የኢትዮጵያ አርት ሙዚየም ለማቋቋም ትልቅ ህልም ነበራቸው፡፡ ለዚሁ ዓላማ ማሳኪያም ንጉሱ አጼ ኃይለ ሥላሴ ቦታ ፈቅደውላቸው ሕንጻውንም ሰርተው አጠናቀው ነበር፡፡

በቢሾፍቱ ከተማ 01 ቀበሌ ውስጥ የሚገኘው የሥነ ጥበብ ማዕከል

ሰዓሊው የሁለት አፍሪቃዊ ጓደኛሞችን የፎቶ ምስል በመሳል በሥራ ላይ እያሉ

ነገር ግን አብዮቱ በፈነዳ በየካቲት ወር 1966 ዓ.ም ማግስት ሰዓሊው ሻምበል ለማ ጉያ ከአየር ኃይል በጡረታ ተሰናበቱ ፡፡ በመቀጠልም በመጋቢት ወር 1967 ዓ.ም የወጣው የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶች በመንግስት ቁጥጥር ሥር የሕዝብ ይዞታ እንዲሆን የወጣው አዋጅ ለሥነ ጥበብ ስራዎቻቸው ማሳያ /gallery / ሰርተው የነበሩትን ሕንጻ በመውረስ ራዕያቸውን አዳፈነው፡፡

ሰዓሊው ግን አሁንም ተስፋ አልቆረጡም፡፡ ሕዝባዊ የነበረውን ማህበራዊ የስርዓት ለውጥ ተቀብለው በቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረትና ኢትዮጵያ መካከል ተቋቁሞ በነበረው የባህል ማዕከል ሥር የኢትዮጵያ ቋሚ ኤግዚቢሽን አስተዳዳሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡ የተለያዩ የፍልስፍና መጻሕፍትንም በአየር ኃይል ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሕዝቡም ውስጥ እንዲሰራጭ ከፍተኛ ትብብር አሳይተዋል፡፡

ሰዓሊው መጽሐፍ ማንበብ ይወዳሉ፡፡ የተለያዩ መጻሕፍትን በማንበብ የዕውቀት አድማሳቸውን ለማስፋት እንደቻሉ ይገልጻሉ፡፡ ሰዓሊው በሚሰሩት የሥዕል ሥራዎቻቸውም ይፈላሰፋሉ፡፡ ለአብነት ያህል እንኳን መጥቀስ ቢያስፈልግ በአንድ ወቅት ባቀረቧቸው ምርጥ የፍራፍሬ ስዕሎች የትዕግስት ፍሬ፣ የነጻነት ፍሬና፣የሠላማዊት ፍሬ የሚል መጠሪያ ሰጥተዋቸው እንደነበር ጸሐፊው ያስታውሳል፡፡ የሶስቱም የፍራፍሬ ሥዕሎች መጠሪያ በመጀመሪያዎቹ ሶስት ሴት ልጆቻቸው ስም ነው፡፡ ሰዓሊው በብሩሻቸው ኢትዮጵያ የነጻነት ተምሳሌትነቷን እንደጠበቀች ፣የሕዝቦቿ ሰላም ተጠብቆ የልማት ፍሬ ናፋቂ ብቻ ሳይሆን ተቋዳሽ እንዲሆን ምኞታቸውን ይገልጹበታል፡፡ እነዚህን ብቻ አይደለም ሌሎችም በርካታ ተፈጥሮን፣ሕብረተሰብን፣ታሪክን እንዲሁም ባሕልና ልማድን አንጸባራቂ የስዕል ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡ በአገሪትዋ ላይ ከሃያ ጊዜያት በላይ ኤግዚቢሽኖችን ለሕዝብ አቅርበዋል፡፡

በጐብኚዎች ዘንድ ልዩ አድናቆትን ካተረፉላቸው ምርጥ የስዕል ሥራዎቻቸው ( notable- works ) መካከልም ቋንጣ፣ አቦል ቡና፣ እሬቻ፣ ዋርካ ፣....ወዘተ የሚል መጠሪያ የተሰጣቸው በአካባቢው ማህበረሰብ ባሕልና ወግ ላይ መሰረት የጣሉ የፈጠራ አብነቶች ይገኛሉ፡፡በተለይም ቋንጣ የተሰኘው እውነታ - ወለድ የስዕል ሥራቸው(realistic art)ሥርዓታትና ዘመናትን ተሻጋሪ በመሆኑ ሊደነቁበት ይገባል፡፡“አንድ ምስል የሺህ ቃላቶችን ያህል ገላጭ ነው ” የሚሉትን የቻይናዎች ብሂላዊ አባባል ቋንጣ በተሰኘው ሥራቸው ሰዓሊው ተጠቅመውበታል፡፡

በወርሃ ግንቦት 1983 ዓ.ም ደርግም ወደቀ፡፡ ኢሕአዴግም መጣ፡፡ ሰዓሊው ሻምበል ለማ ጉያም አዲስ ራዕይ ታያቸው፡፡ ራዕይ የፈጠራ ሰውን አነሳሽ ፣ ቀስቃሽም ኃይል ነውና፡፡

ሰዓሊው ከአስር ዓመት የፈጠራ ሥራና ድካም በኋላ በጥቅምት ወር 1993 ዓ.ም በዚችው በሚኖሩባት ቢሾፍቱ በመልክዓ ምድር ጸጋዋ የሰባት ሐይቆች ምድር ፣ አድማስዋን ተንተርሰው ዙሪያዋን ጉብ ጉብ ባሉ የየረር፣ የዝቋላ፣ የጋራ በሩ እና የበደገባቤ ጋራዎች ተከባ፣ በተጨማሪም በአረንጓዴ ለም እጽዋት የተፈጥሮ ውበት ደምቃ፣ እንዲሁም በነዋሪዎቿ ሰው አፍቃሪነትና እንግዳ ተቀባይነት የባሕል መኩሪያ በሆነችው የደብረ ዘይት ከተማ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካን የኪነ ጥበብ ሙዚየም ለማቋቋም ተነሱ፡፡ሰዓሊው ይህን ሙዚየም የከፈቱት ለመኖሪያ ቤት መስሪያና ለዚሁ ቅዱስ ዓላማ ማሳኪያ በተሰጣቸው የአስር ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ነው፡፡ ታዲያ ይህን የሥነ ጥበብ ማዕከል ለመጎብኘት ወደ ግቢው ሲዘልቁ በአፍሪካነትዎ የሚኮሩበትን የዘርና የቀለም መድልዎን ተፋላሚ፣ አፍሪካዊውን የነጻነት አባት፣ የህብረዝርያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መስራች[2] የኔልሰን ማንዴላን ሐውልት በአፍሪካ ካርታ ላይ በልዩ ድንጋይ ተቀርጾ ቀኝ እጁን ወደ ላይ ከፍ አድርጎ በሰላምታና በፈገግታ የሚቀበልዎ ምስል ሲመለከቱ መንፈስዎ በማያውቁት የጥበብ ዓለም ውስጥ ይመሰጣል፡፡

ሰዓሊው ወደፊት አሻግሮ የሚያራምድ ታላቅ ራዕይ ያላቸው ትልቅ የጥበብ ሰው ናቸው፡፡ በሙዚየሙ ቅጥር ግቢ ውስጥ የማንዴላን ሐውልት ያቆሙት በማንዴላ የሕይወት ዘመናቸው ነው፡፡ እንደ ግለሰብ ድንቅ ተግባር ነው፡፡ ማንዴላ በኢትጵያዊነት መንፈስ ተሞልተው ከኢትዮጵያውያን አፍቃሪ ነጻነትን፣ ትዕግስተኝነትንና ቻይነትን ሲማሩ ፣ ሰዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ ደግሞ ከማንዴላ መንፈስ ውስጥ የዓላማ ጽናትን፣ ይቅር ባይነትና ሰላም ወዳድነትን ወስደው ላገራቸውም ይህንን ራዕይ የተመኙ ይመስለኛል፡፡እ.ኤ.አ ኦክቶበር 21 ቀን 2000 ዓ.ም የዚያን ወቅት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ሳሊም አህመድ ሳሊም በመክፈቻው ቀን ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ባደረጉት ንግግር እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

“ይህንን የአፍሪካ ኪነ ጥበብ ሙዚየም መጎብኘቴን እንደ ትልቅ ዕድል እቆጥረዋለሁ፡፡ ይህንን ዕድል በማግኘቴም ደስተኛ ነኝ፡፡ ለታላቁ አፍሪካዊ ለኔልሰን ማንዴላ ወደ ነጻነት ረጅም የሕይወት ጉዞ ልዩ ዋጋ የሚሰጥ ሥፍራ ነው፡፡ ለታዋቂው ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊ አርቲስት ሻምበል ለማ ጉያ ለዚህ ተግባር በመሪነታቸውና ለራዕያቸውም አድናቆቴን ልገልጽላቸው እወዳለሁ፡፡[3] ” ሌሎችም በርካታ የአፍሪካ አገር መሪዎችና አምባሳደሮች ማዕከሉን ጎብኝተው የተደሰቱና ቅን አስተሳሰባቸውን የተረዱ የሞራል ድጋፋቸውን ለግሰዋቸዋል፡፡ለወደፊቱም ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች የሥዕልና የቅርጻ ቅርጽ ሥራዎቻቸውን ወደ ሙዚየሙ ለማምጣት ቃል ቢገቡም በገቢር ግን ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡

ሰዓሊ ለማ ጓያ የራሳቸውን ምስል በፍየል ቆዳ ላይ ከሳሉት

ሰዓሊው ግን አሁንም በድጋሚ እንዳሰቡት ዕቅዳቸው ባይሟላም የሙዚየሙነቱን መጠሪያ በመተው በስማቸው“ ለማ ጉያ የሥነ ጥበብ ማዕከል ” ስያሜ በመስጠት ስኬታማ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ የሥነ ጥበብ ማዕከላቸው ውስጥም አራት የስዕል ሥራዎቻቸውን ማስጎብኛ ክፍሎች (art gallery) ይገኛሉ፡፡

ሰዓሊው በብሩሽና ቀለማቸው ከቢሽፍቱ ሐይቆች እስከ ዓባይ ጢስ ፏፏቴ፣ ከአፋርዋ ወጣት እስከ ኦሮምያዊቷ ኮረዳ፣ ከላሊበላ ግንብ እስከ አክሱም ሐውልት፣ ከአዕዋፋት እስከ ዱር እንሰሳት፣ ከማራቶኑ ጀግና አበበ ቢቂላ እስከ ኃይሌ ገ/ሥላሴ፣ የአንድነት አባት ከሆኑት አጼ ቴዎድሮስ እስከ የበረሃው አርበኛ መለስ ዜናዊ፣ ካገሬ ገበሬ እስከ የፊዚክሱ ሊቅ አልበርት አንስታይን እና የታላላቅ የአፍሪካ ስመ ጥር መሪዎች ምስልም በሥዕል ሥራዎቻቸው ይገኛሉ፡፡

ሰዓሊው የፈጠራ ሥራዎቻቸውን በወረቀት፣ በፋይዝት ቦርድ፣ በጋቢና በሸራ እንዲሁም በጨርቅም ላይ በመሳል ልዩ ክህሎት አላቸው፡፡ በይበልጥ ደግሞ ሰዓሊውን ከሌሎች የዚህ ጥበብ ባለቤቶች ለየት የሚያደርጋቸው ባገራችንና በመላው አፍሪካ በፍየል ቆዳ ላይ በመሳል የተካኑ በመሆናቸው ነው፡፡ቀደም ሲል በቆዳና በብራና ላይ የተሰሩ በርካታ የፈጠራ ሥራዎች መኖራቸው የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ ነገር ግን ጸጉር ባለው የፍየል ቆዳ ላይ ሥዕልን በመሥራት ጀማሪው እሳቸው ናቸው፡፡ በዚህም የፈጠራ ውጤታቸው በኢትዮጵያ የሥነ ጥበባት አምባ ውስጥ ባገር አቀፍ ደረጃ ለፈጠራ ሥራዎች ዕድገት የበኩላቸውን ከፍተኛ ድርሻ አበርክተዋል ማለት ይቻላል፡፡

ዛሬ የሰዓሊውን የሥነ ጥበብ ማዕከል በሩ ክፍት ሆኖ የሚጎበኙት አምባሰደሮችና የአፍሪካ መሪዎች ብቻ አይደሉም፡፡ መጪው ትውልድ ሁሉ ሥራቸውን እንዲጎበኘው በራቸው ክፍት ነው፡፡ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችና ከልዩ ልዩ ትምህርት ቤቶች ትምህርታዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደዚሁ ማዕከል ይመጣሉ፡፡በአገሪቱ መደበኛ ት/ት ቅርጽ ያልያዘውን የጥበብ አቅጣጫ ፈር ለማስያዝ መልካም ጅምር ነው፡፡

ሰዓሊው አንድ ናይጄሪያዊም ሰዓሊ ወደዚሁ የሥነ ጥበብ ማዕከላቸው መጥቶ ይህንኑ የሳቸውን ፈጠራ እንዳስተማሩትና ልምዳቸውንም አካፍለውት ከተመለሰም በኋላ ዛሬ በምዕራብ አፍሪካ ውስጥ በሳቸው የፈጠራ ስታይል የሚሰራ እርሱ ብቻ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ሰዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ እንደነ ስፔኒያዊው የአለማችን እውቁ ሰዓሊ ፓብሎ ፒካሶ የስዕል ጥበብ ሙያን ከአባቱ ሰዓሊና የስዕል መምህር ሩይዝ ብላስኮ እንደቀሰመው[4] ወይንም ደግሞ እንደ እውቁ የአለማችን የሙዚቃ አቀናባሪ ቮልፍጋንግ አማዱስ ሞዛርት ገና በአራት ዓመቱ ፒያኖ መጫወትና ኖታን የማንበብ ጸጋ እንዳለው እንዲታወቅ የቫዮሊን ሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችና መምህር የነበረው አባቱ ሊዎፖልድ ሞዛርት ቁልፍ ሚና እንደተጫወተው ሁሉ[5]በእኚህ ሰዓሊ ግን የዚህ ዓይነቱን ዕድል አልነበራቸውም፡፡ በተፈጥሮ ጸጋቸው ላይ ብቻ ተመርኩዘው ራሳቸውን በራሳቸው በማስተማር( self-taught )አርቲስት በመሆናቸው እንደ ዘመኑ ሰዓሊዎች በሥነ ጥበብ አካዳሚ ገብተው የመማር ዕድሉም ሳይገጥማቸው በግል ጥረታቸው ለዚህ አገራዊና አህጉራዊ እውቅናን ለማግኘት መቻላቸው እጅግ የሚያስደንቅ ነው፡፡ታላቅ ንጥረ አፍሪካዊ የጥበብ ሰው ናቸው፡፡

ሰዓሊው ለሙያቸው ያላቸው ፍቅርና የፈጠራ ጥማት ልዩ ነው፡፡ ምንም እንኳን በዕድሜያቸው 85ኛ ዓመታቸው ላይ ቢደርሱም በአካልም ሆነ በመንፈሳቸው ላይ ድካም ፈጽም አይታይባቸውም፡፡ ብሩሽና ቀለም ከእጃቸው ለአፍታ እንኳን አይለያቸውም፡፡ ሰዓሊው ይስላሉ፣ ዛሬም ይስላሉ፣ ነገም ይስላሉ፣ ወደፊትም ይስላሉ… በተለይም የፎቶን ምስል መልሰው አሳድገው በቆዳ ላይ በመሳል በ visual partrait ይታወቃሉ፡፡ የፈጠራ ውጤት ሥራዎቻቸው ዛሬ በሚኖሩበት ቢሾፍቱ ከተማ የሥነ ጥበብ ማዕከላቸው ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባና እንዲሁም በባሕር ዳር ከተማ የአማራ ብሔራዊ ክልል የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት በሚገኝበት ቦታ ላይ በተሰራው የስዕል ማሳያ አዳራሽ ( art gallery ) ውስጥ ከሌሎች ሰዓሊዎች ጎን ለአብነት ያህል ስማቸውን ለመጥቀስ ከእነ ገብረክርስቶስ ደስታ፣ ስዩም አያሌው፣ ሰብስቤ ገ/ሥላሴ፣ አበበ ደስታ፣ አስናቀ መለስ፣ ማርቆስ በቀለ...ወዘተ ጋር በመሆን ሥራዎቻቸው በግንባር ቀደምትነት በመጎብኘት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሰዓሊው ወደፊት በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልም ቅርንጫፍ የሥነ ጥበብ ማዕከላቸውን የማቋቋም ዕቅድ አላቸው፡፡ በሥነ ጥበብ ዓለም ውስጥ ያካበቱትን ሰፊ የፈጠራ ስራዎች ልምድ ለጀማሪና ለወጣት ሰዓሊያን ለማስተላለፍም ዕቅድ አላቸው፡፡ “ ብዙ መጻህፍትን ከውጭ ያስመጣሁት ለዚሁ ዓላማ ነው፡፡ ” ይላሉ፡፡ አሁን ያለውና ወደፊትም የሚመጣው ወጣት ትውልድ እንዲጠቀምባቸው በአገሪቷ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች የስዕል መማሪያ መጽሐፍ እያሰናዱ መሆናቸውንና በቅርቡም በገበያ እንደሚውሉ ይገልጻሉ፡፡ከዚህ በፊትም ካንዴም ሁለት ጊዜ “ ያለ አስተማሪ የስዕል ጥበብ መማሪያ ” የሚል መጽሐፎችን አሳትመዋል፡፡ የስዕል ሥራውቻቸውን ከአገር ውጭም በአፍሪካ አገራት በኬንያ፣በሴኔጋልና በናይጄሪያ ፣በአውሮፓ ደግሞ በስዊድንና በእንግሊዝ፣እንዲሁም በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማኤግዚቢሽኖችን ለጎብኚዎች አቅርበዋል፡፡ሰዓሊው ይህንኑ የጥበብ ሙያቸውንና ልምዳቸውን ለልጆቻቸው ለማስተላለፍም ታድለዋል ፡፡ ሶስቱ ሴት ልጆቻቸው ትዕግስት፣ነጻነትና ሰላማዊት በኒውዮርክ የስዕል ኤግዚቢሽኖችን ያቀርባሉ፡፡ በተለይም የራሳቸውን የፈጠራ ጥበብ በ modern style ለማቅረብ “ ነጻነት አርት ስቱዲዮ ” ከፍተዋል፡፡ በአገር ውስጥም ሁለት ወንድ ልጆች አላቸው፡፡ ደረጀ የተባለው ልጃቸው በፎቶ ጥበብ ሙያ ላይ ይሰራል፡፡ዳዊት የተባለው የመጨረሻ ወንድ ልጃቸውም በናይጄሪያ የስዕል ሙያ ትምህርቱን አጠናቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሰዓሊው ሁለት ታናሽ ወንድሞችም እንደዚሁ የኪነ ጥበብ ሰዎች ናቸው፡፡አንደኛው ቱሉ ጉያ ከአ.አ ሥነ ጥበብት/ቤት ተመርቀው የስዕል መምህር ናቸው፡፡ ሌላኛው አሰፋ ጉያ ደግሞ ደራሲ ናቸው፡፡ ድንቅ ቤተሰባዊ “የጥበብ ጉያዎች” ናቸው፡፡

ስለ ሰዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ ሥራዎች በአገር ውስጥ በተለያዩ አዘጋጆች የተለያዩ ሜዲያ ሽፋን ብቻም ሳይሆን፣ በውጭ አገርም ሶሻል ሜዲያ ኔትዎርክስ ከፍተኛ ሽፋን አግኝተዋል፡፡

በአገር ውስጥና በውጭ አገርም ከፍተኛ እውቅና ከማግኘታቸውም በላይ ምስጋናና ሽልማቶችንም ተቀብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት 2005 ዓ.ም ላይ በሰሜን አሜሪካ የውርስና ቅርስ ማህበር ባደረገላቸው ጥሪ ላይም ተገኝተው ለሥራቸው ሽልማት አበርክተውላቸዋል፡፡

ማጠቃለያ፣ ሰዓሊው በዚህ ሁኔታ ድፍን ለግማሽ ክፍለ ዘመን ከኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ዓለም እንዳልተለያዩ እንረዳለን፡፡በአገር አቀፍና አህጉር አቀፍ ደረጃም በፍየል ቆዳ ላይ የቅብ ስዕል ስራ በጀማሪነታቸው የራሳቸውን የጥበብ አሻራ አስቀምጠዋል፡፡ ስዕልን ለመማር የተፈጥሮ ዝንባሌ ላላቸው ወጣቱ ትውልድ ያለ አስተማሪ የስዕል መማሪያ የሚሆን ሁለት መጽሐፍት አሳትመዋል፡፡ይህም ለኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር የስዕል መማሪያ መርጃ በማቅረብ እገዛ አድርገዋል፡፡ስለዚህ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የእኚህን ሰዓሊ ታላላቅ ጥረቶች ግምት ውስጥ በማስገባት ለድካማቸውና ለፈጠራ ሥራ ማበረታቻ ይሆን ዘንድ በአ.አ.ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክተሬት ሰጪ ኮሚቴ ሊያስብበት ይገባዋል ሲል በአክብሮት ያሳስባል፡፡

 

 

ዋቢ መረጃዎች፣

1/ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር፥ የካቲት 1993፡፡አማርኛ መዝገበ ቃላት፡፡አዲስ አበባ፡፡ ገጽ 131

2/ Freedom Fighters. Politicians, Religious leaders, Ordinary Men...,By Anne Williams 2007 p.547-553

3/ የአፍሪካ ጥበባት ማዕከል ራዕይ፡፡ በግርማቸው /ጽዮን . ሪፖርተር መጽሔት. ታህሳስ 1993, ቅጽ 4. 32. ገጽ 27

4/ Early Life Pablo Picasso, wikipedia, The Free Encyclopedia, online

5/ Wolfgang Amadous Mozart, 2000, Schott Music Instrumental,Mainz- Germany

ጸሐፊውን በኢሜይል : gez.dinku2@gmail.com ማግኘት ይችላሉ፡፡ የካቲት 8 ቀን 2006 .( 15.02.2014 )

 

                                                              Copyright ©2008 GPO/OPC Allrights Reserved